English

ምዕራፍ 28

1አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ።
2ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ።
3ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።
4እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።
5ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም።
6የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን።
7እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።
8እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው።
9ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።