English

ምዕራፍ 29

1የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ።
2የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።
3የእግዚአብሔር ድምፅ በውኆች ላይ፥ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ።
4የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ በታላቅ ክብር ነው።
5የእግዚአብር ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል።
6እንደ ጥጃ ሊባኖስን፥ አንድ ቀን እንዳለው አውሬ ልጅ ስርዮንን ያዘልላቸዋል።
7የእግዚአብሔር ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል።
8የእግዚአብሔር ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ እግዚአብሔር የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል።
9የእግዚአብሔር ድምፅ ዋላዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ጫካዎቹንም ይገልጣል፤ ሁሉም በመቅደሱ። ምስጋና ይላል።
10እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል።
11እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።