ምዕራፍ 34
1እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው።
2ነፍሴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፥ ገሮችም ሰምተው ደስ ይላቸዋል።
3እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ።
4እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ።
5ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም።
6ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።
7የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።
8እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።
9የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት።
10ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉትን ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም።
11ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።
12ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ?
13አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ።
14ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም።
15የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።
16መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው።
17ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው።
18እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
19የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።
20እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።
21ኃጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ።
22የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል፥ በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ አይጸጸቱም።