English

ምዕራፍ 33

1ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል።
2እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት።
3አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤
4የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና።
5ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።
6በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤
7የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው።
8ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ።
9እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም።
10እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል።
11የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው።
12እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ።
13እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ።
14ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥
15እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል።
16ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም።
17ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም።
18እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥
19ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ።
20ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና።
21ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና።
22አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።