ምዕራፍ 36
1ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም።
2በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል።
3የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው፤ ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ።
4በመኝታው ጠማማነትን አሰበ፤ መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፤ ክፋትን አይንቃትም።
5አቤቱ፥ ምሕረትህ በሰማይ ነው፥ እውነትህም ወደ ደመናት ትደርሳለች።
6ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች፥ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት፤ አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ።
7አቤቱ፥ ምሕረትህን እንዴት አበዛህ! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ።
8ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ፥ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ።
9የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።
10ምሕረትህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ።
11የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የኃጢአተኞችም እጅ አያውከኝ።
12ዓመፃን የሚያደርጉ ሁሉ ከዚያ ወደቁ፤ ወድቀዋል፥ መቆምም አይችሉም።