English

ምዕራፍ 37

1በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤
2እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና።
3በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ።
4በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
5መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል።
6ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል።
7ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።
8ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።
9ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።
10ገና ጥቂት፥ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።
11ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።
12ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለካከተዋል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል።
13እግዚአብሔር ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና።
14ኃጢአተኞች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፤
15ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር።
16ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ከኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል።
17የኃጥአን ክንድ ትሰበራለችና፤ እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል።
18የንጹሓንን መንገድ እግዚአብሔር ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘላለም ነው፤
19በክፉ ዘመንም አያፍሩም በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።
20ኅጥአን ግን ይጠፋሉ፥ የእግዚአብሔር ጠላቶች በከበሩና ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ እንደ ጢስ ይጠፋሉ።
21ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም።
22እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፤ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ።
23የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል።
24ቢወድቅም ለድንጋፄ አይጣልም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና።
25ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም።
26ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል።
27ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ለዘላለምም ትኖራለህ።
28እግዚአብሔር ፍርዱን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኅጥኣን ዘር ግን ይጠፋል።
29ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
30የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
31የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም።
32ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል።
33እግዚአብሔር ግን በእጁ አይተወውም፥ በተፋረደውም ጊዜ አያሸንፈውም።
34እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።
35ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት።
36ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም።
37ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና።
38በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።
39የጻድቃን መድኃኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው።
40እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከኃጢአተኞችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋል፥ በእርሱ ታምነዋልና።