English

ምዕራፍ 44

1አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን።
2እጅህ አሕዛብን አጠፋች፥ እነርሱንም ተከልህ፤ አሕዛብን ሣቀይኻቸው አሳደድኻቸውም።
3በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፤ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ ወድደሃቸዋልና።
4አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤ ለያዕቆብ መድኃኒትንህ እዘዝ።
5በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።
6በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፤
7አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው።
8ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን።
9አሁን ግን ጠላኸን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም።
10ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን።
11እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን።
12ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም።
13ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።
14በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ የራስ መንቀሳቀሻ አደረግኸን።
15ጕስቍልናዬ ሁልጊዜም በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ።
16ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው።
17ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም።
18ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፤
19በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና።
20የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥
21እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና።
22ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል።
23አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን።
24ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ?
25ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና።
26አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ስምህም ተቤዠን።