English

ምዕራፍ 45

1ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው።
2ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፤ ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ።
3ኃያል ሆይ፥ በቍንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ።
4ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፤ ቀኝህም በክብር ይመራሃል።
5ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ።
6አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘላለም ነው፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።
7ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።
8በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፤ ከዝሆን ጥርሶች አዳራሽ ደስ ያሰኙሃል።
9የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
10ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤
11ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና።
12የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ።
13ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፤ ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው።
14በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፤
15በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥ ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል።
16በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ።
17ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፤ ስለዚህ ለዓለምና ለዘላለም አሕዛብ ይገዙልሃል።