ምዕራፍ 55
1አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል።
2ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤
3ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና።
4ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ።
5ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ።
6በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ!
7እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤
8ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።
9አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ።
10በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤
11ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም።
12ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።
13አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤
14መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን።
15ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና።
16እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ።
17በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል።
18በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት።
19ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል።
20ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ።
21አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው።
22ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።
23አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።