ምዕራፍ 56
1አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፤ ሁልጊዜም በሰልፍ አስጨንቆኛል።
2የሚዋጉኝ በዝተዋልና ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ።
3እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ።
4በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?
5ሁልጊዜ ቃሎቼን ያጸይፉብኛል፤ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው።
6ይሸምቁብኛል ይሸሽጉኝማል፥ እነርሱም ተረከዜን ይመለካከታሉ፥ ሁልጊዜም ነፍሴን ይሸምቁባታል።
7በምንም ምን አታድናቸውም፤ አሕዛብን በቍጣ ትጥላቸዋለህ።
8አምላክ ሆይ፥ ሕይወቴን ነገርሁህ፤ እንባዬን እንደ ትእዛዝህ በፊተህ አኖርህ።
9በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ።
10በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ።
11በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?
12አቤቱ፥ የምስጋና ስእለት የምሰጥህ ከእኔ ዘንድ ነው፤
13ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ።