English

ምዕራፍ 57

1ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ጉዳት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ።
2ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።
3ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ።
4ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው።
5አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።
6ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ።
7ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ።
8ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ።
9አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤
10ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ።
11አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።