English

ምዕራፍ 72

1አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥
2ሕዝብህን በጽድቅ፥ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ።
3ተራሮችና ኰረብቶች ለሕዝብህ ሰላምን ይቀበሉ።
4ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ትፈርዳለህ የድሆችንም ልጆች ታድናለህ፤ ክፉውንም ታዋርደዋለህ።
5ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለፊት ለልጅ ልጅ ይኖራል።
6እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይወርዳል።
7በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው።
8ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።
9በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።
10የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።
11ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል።
12ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና።
13ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፥ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።
14ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው።
15እርሱ ይኖራል ከዓረብም ወርቅ ይሰጡታል፤ ሁልጊዜም ወደ እርሱ ይጸልያሉ፥ ዘወትርም ይባርኩታል።
16በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።
17ስሙ ለዘላለም ቡሩክ ይሆናል፥ ከፀሐይም አስቀድሞ ስሙ ይኖራል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ይባረካሉም አሕዛብ ሁሉ ያመሰግኑታል።
18ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ።
19የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። ይሁን፤ ይሁን።
20የእሴይ ልጅ የዳዊት መዝሙር ተፈጸመ።