ምዕራፍ 73
1ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው።
2እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ።
3የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።
4ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና።
5እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም።
6ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት።
7ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ።
8አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ።
9አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ።
10ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤
11እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ።
12እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።
13እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ።
14ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው።
15እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር።
16አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ።
17ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ።
18በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው።
19እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ።
20ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።
21ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤
22እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ።
23እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ።
24በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ።
25በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ?
26የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው።
27እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው።
28ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።