ምዕራፍ 77
1በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ።
2በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም።
3እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች።
4ዓይኖቼ እንዲተጉ ያዝሃቸው፤ ደነገጥሁ አልተናገርሁም።
5የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም
6በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት።
7እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን?
8ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን?
9እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?
10ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ።
11የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤
12በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ።
13አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
14ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልን አስታወቅሃቸው።
15የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው።
16አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ።
17ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ።
18የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም።
19መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም።
20በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።