ምዕራፍ 78
1ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።
2አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ፥ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ።
3የሰማነውንና ያውቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም።
4የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ።
5ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፤
6የሚመጣ፥ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ፤
7ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤
8እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።
9የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።
10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤
11መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥
12በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት።
13ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ክምር አቆመ።
14ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።
15ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው።
16ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ።
17ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት።
18ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት።
19እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?
20ዓለቱን መታ፤ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፤ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?
21እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፤
22በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በመድኃኒቱም አልተማመኑምና።
23ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤
24ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው።
25የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው።
26ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፤
27ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤
28በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ።
29በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።
30ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥
31የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።
32ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፤
33ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ።
34በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤
35ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ሆነ አሰቡ።
36በአፋቸው ብቻ ወደዱት፤ በአንደበታቸውም ዋሹበት፤
37ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም።
38እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።
39ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ።
40በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት።
41ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።
42እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥
43በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን።
44ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ።
45ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤ በጓጉንቸርም አጠፋቸው።
46ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።
47ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ።
48እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ።
49የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ።
50ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤
51በኵሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ።
52ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው።
53በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው።
54ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚህች ተራራ፤
55ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ።
56ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤
57ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤
58በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት።
59እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤
60የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤
61ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ።
62ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ ርስቱንም ቸል አላቸው።
63ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ቈነጃጅቶቻቸውም አላዘኑም፤
64ካህናቶቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም።
65እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤
66ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘላለምን ኀሣር ሰጣቸው።
67የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤
68የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ።
69መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።
70ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤
71
72