ምዕራፍ 81
1በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ።
2ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፤
3በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤
4ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ።
5ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ።
6ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ።
7በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ በተሰወረ ዐውሎም መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ።
8ሕዝቤ ሆይ፥ስማኝ እነግርሃለሁም፤ እስራኤል ሆይ፥ እመሰክርልሃለሁ።
9አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም።
10ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም።
11ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም።
12እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ።
13ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፤
14ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፤
15የእግዚአብሔር ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘላለም በሆነ ነበር፤
16ከስንዴም ስብ ባበላቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር።