English

ምዕራፍ 80

1ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ።
2በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም፤ ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና።
3አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።
4የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ በባሪያህ ጸሎት ላይ እስከ መቼ ትቈጣለህ?
5የእንባ እንጀራን ትመግበናለህ፥ እንባም በስፍር ታጠጣናለህ።
6ለጎረቤቶቻችን ክርክር አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም በላያችን ተሣለቁብን።
7የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።
8ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ።
9በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች።
10ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ።
11ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች።
12አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል።
13የዱር እርያ አረከሳት፥ የአገር አውሬም ተሰማራባት።
14የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ።
15በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኸውን ቀኝህ የተከላትን አንሣ።
16በእሳት ተቃጥላለች ተነቅላማለች፤ ከፊትህ ተግሣጽም የተነሣ ይጠፋሉ።
17ለአንተ ባጸናኸው በሰው ልጅ ላይ፥ በቀኝህ ሰው ላይ እጅህ ትሁን።
18ከአንተም አንራቅ፤ አድነን ስምህንም እንጠራለን።
19የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።