English

ምዕራፍ 83

1አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል።
2እነሆ፥ ጠላቶችህ ጮኽዋልና፥ የሚጠሉህም ራሳቸውን አንሥተዋልና።
3ሕዝብህን በምክር ሸነገሉአቸው፥ በቅዱሳንህም ላይ ተማከሩ።
4ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፥ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ።
5አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ፤ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፤
6የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም፥ ሞዓብም አጋራውያንም፥
7ጌባል አሞንም አማሌቅም፥ ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋር፤
8አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ፥ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ሆኑአቸው።
9እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፥ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው።
10በዓይንዶር ጠፉ፥ እንደ ምድርም ጕድፍ ሆኑ።
11አለቆቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ፥ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸው።
12የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንወርሳለን የሚሉትን።
13አምላኬ ሆይ፥ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው።
14እሳት ዱርን እንደሚያቃጥል፥ ነበልባልም ተራሮች እንደሚያነድድ፥
15እንዲሁ በቍጣህ አሳድዳቸው፥ በመቅሠፍትህም አስደንግጣቸው።
16ፊታቸውን እፍረት ሙላው፥ አቤቱ፥ ስምህንም ይፈልጋሉ።
17ይፈሩ ለዘላለሙም ይታወኩ፤ ይጐስቍሉ ይጥፉም።
18ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፥ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።