English

ምዕራፍ 84

1የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!
2ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፤ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ።
3ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች፥ ዋኖስም ጫጩቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፥ እርሱ መሠዊያህ ነው።
4በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል።
5አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው።
6በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና።
7ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።
8የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ አድምጥ።
9አቤቱ፥ መታመናችንን እይልን፥ ወደ ቀባኸውም ፊት ተመልከት።
10ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።
11እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም።
12የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው።