ምዕራፍ 86
1አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።
2ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።
3አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።
4የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።
5አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።
6አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።
7ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።
8አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።
9ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፤
10አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
11አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።
12አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤
13ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።
14አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፤ በፊታቸውም አላደረጉህም።
15አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ፤
16ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።