English

ምዕራፍ 85

1አቤቱ፥ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ።
2የሕዝብህን ኃጢአት አስቀረህ፥ አበሳቸውንም ሁሉ ከደንህ።
3መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፤ ከቍጣህ መቅሠፍት ተመለስህ።
4የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቍጣህንም ከእኛ መልስ።
5በውኑ ለዘላለም ትቈጣናለህን? ቍጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን?
6አቤቱ፥ ትመለሳለህ ታድነንማለህ፤ ሕዝቡም በአንተ ደስ ይላቸዋል።
7አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህንም ስጠን።
8እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና።
9ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው፤
10ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ።
11እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች።
12እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል፥ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች።
13ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፥ ፍለጋውንም በመንገድ ውስጥ ያኖራል።