English

ምዕራፍ 88

1አቤቱ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ በቀንና በሌሊት በፊትህ ጮኽሁ፤
2ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፤
3ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና።
4ወደ ጓድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ።
5ለዘላለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፤ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ።
6በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጕድጓድ አስቀመጥኸኝ።
7በእኔ ላይ ቍጣህ ጸና፥ መቅሠፍትህን ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ።
8የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅህ፤ በእነርሱ ዘንድ ርኵስ አደረግኸኝ፤ ያዙኝ፥ መውጫም የለኝም።
9ዓይኖቼም በመከራ ፈዘዙ፤ አቤቱ፥ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ፥
10በውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለህን? የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን?
11በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን?
12ተአምራትህ በጨለማ፥ ጽድቅህንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን?
13አቤቱ፥ እኔ ግን ወደ አንተ ጮኽሁ፤ በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች።
14አቤቱ፥ ነፍሴን ለምን ትጥላለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?
15እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብሁ ነኝ፤ ከፍ ከፍ ካልሁ በኋላ ግን ተዋረድሁ ተናቅሁም።
16መቅሠፍትህ በላዬ አለፈ፥ ግርማህም አስደነገጠኝ።
17ሁልጊዜ እንደ ውኃ ከበቡኝ፥ በአንድነትም ያዙኝ።
18ወዳጄንና ባልንጀራዬን ዘመዶቼንም ከመከራ የተነሣ ከእኔ አራቅህ።