English

ምዕራፍ 89

1አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘላለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ።
2እንዲህ ብለሃልና። ምሕረት ለዘላለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል።
3ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ።
4ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ።
5አቤቱ፥ ሰማያት ተኣምራትህን እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ።
6እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል?
7በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው።
8አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል።
9የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ።
10አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው።
11ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትህ።
12ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል።
13ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች።
14የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።
15እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ።
16በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤
17የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።
18ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና።
19በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ እንዲህም አልህ። ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ።
20ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት።
21እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች።
22ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም።
23ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ።
24እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል።
25እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ።
26እርሱ። አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል።
27እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል።
28ለዘላለምም ምሕረቴን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው።
29ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ።
30ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፤
31ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፤
32ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ።
33ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፤
34ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም።
35ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ።
36ዘሩ ለዘላለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል።
37ለዘላለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፤ ምስክርነቱ በሰማይ የታመን ነው።
38አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ የቀባኸውንም ጣልኸው።
39የባሪያህንም ኪዳን አፈረስህ፥ መቅደሱንም በምድር አረከስህ።
40ቅጥሩን ሁሉ ጣልህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ።
41መንገድ አላፊም ሁሉ ተናጠቀው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ።
42የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ።
43የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም።
44ከንጽሕናውም ሻርኸው፥ ዙፋኑንም በምድር ጣልህ።
45የዙፋኑንም ዘመን አሳነስህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው።
46አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ፊትህን ትመልሳለህ? እስከ መቼስ ቍጣህ እንደ እሳት ይነድዳል?
47ችሎታዬ ምን እንደ ሆነ አስብ፤ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን?
48ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው?
49ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ምሕረትህ ወዴት ነው?
50አቤቱ፥ የባሪያዎችህን ስድብ፥ በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥
51አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን የቀባኸውን ዘመን የሰደቡትን አስብ።
52እግዚአብሔር ለዘላለም ይባረክ። ይሁን ይሁን።