ምዕራፍ 96
1ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
2እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ፥ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ።
3ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤
4እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና።
5የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
6ምስጋናና ውበት በፊቱ፥ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።
7የአሕዛብ ወገኖች፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤
8ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባን ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ።
9በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጥ።
10በአሕዛብ መካከል። እግዚአብሔር ነገሠ በሉ። እንዳይናወጥም ዓለሙን እርሱ አጸናው፥ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።
11ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ፤
12በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤
13ይመጣልና፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።