ምዕራፍ 97
1እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ሐሤትን ታድርግ፥ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው።
2ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።
3እሳት በፊቱ ይሄዳል፥ ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል።
4መብረቆቹ ለዓለም አበሩ፤ ምድር አየችና ተናወጠች።
5ተራሮችም ከእግዚአብሔር ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።
6ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ።
7ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት።
8አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው፤
9አንተ፥ እግዚአብሔር፥ በምድር ላይ ሁሉ ልዑል ነህና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃልና።
10እግዚአብሔርን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል።
11ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።
12ጻድቃን፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።