ምዕራፍ 11
1አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።
2ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።
3ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች።
4በቍጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች።
5የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኃጥእ ግን በኃጢአቱ ይወድቃል።
6ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ።
7ኀጥእ በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል።
8ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ኀጥእም በእርሱ ፋንታ ይመጣል።
9ዝንጉ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ።
10በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በኀጥኣንም ጥፋት እልል ትላለች።
11በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኀጥኣን አፍ ግን ትገለበጣለች።
12ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል።
13ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፤ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል።
14መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል።
15ለማያውቅ የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፤ ዋስነትን የሚጠላ ግን ይድናል።
16ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ሀኬተኖችም ሀብትን ያገኛሉ።
17ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል።
18የኀጥእ ሰው ሞያ ሐሰተኛ ነው፤ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው።
19በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው።
20ልበ ጠማሞች በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፤ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው።
21ክፉ ሰው እጅ በእጅ ሳይቀጣ አይቀርም፤ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል።
22የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት።
23የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው።
24ያለውን የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም።
25የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል።
26እህልን የሚያስቀር ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፤ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው።
27መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፤ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል።
28በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ።
29ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፥ ሰነፍም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል።
30የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው።
31እነሆ፥ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፥ ይልቁንስ ኀጥእና ዓመፀኛ እንዴት ይሆናሉ!