English

ምዕራፍ 12

1ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው።
2ደኅና ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ሰው ግን ይቀሥፈዋል።
3ሰውን ዓመፃ አያጸናውም፤ የጻድቃን ሥር ግን አይንቀሳቀስም።
4ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት።
5የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ የኃጥኣን ምክር ግን ተንኰል ነው።
6የኃጥኣን ቃል ደምን ለማፍሰስ ትሸምቃለች፤ የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።
7ኀጥኣን ይገለበጣሉ፥ ደግሞም አይገኙም፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።
8ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል።
9ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል።
10ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው።
11ምድሩን የሚሠራ ሰው እንጀራ ይጠግባል፤ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን አእምሮ የጐደለው ነው።
12የኅጥኣን ፈቃድ የክፉዎች ወጥመድ ናት፤ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል።
13ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል።
14የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል።
15የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል።
16የሰነፍ ቍጣ ቶሎ ይታወቃል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል።
17እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፤ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል።
18እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።
19የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው።
20ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፤ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው።
21ጻድቅን መከራ አያገኘውም፤ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው።
22ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።
23ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፤ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።
24የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።
25ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።
26ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች።
27ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፤ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው።
28በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።