ምዕራፍ 13
1ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል። ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
2ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች።
3አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋትን ያገኘዋል።
4የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች።
5ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም።
6በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፤ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል።
7ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፤ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው።
8ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
9ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል።
10በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት።
11በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች።
12የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።
13ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፤ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል።
14ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው።
15መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፤ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት።
16ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል።
17መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው።
18ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል።
19የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፤ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ።
20ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።
21ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፤ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ።
22ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች።
23በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፤ ከፍርድ መጕደል የተነሣ ግን ይጠፋል።
24በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጻዋል።
25ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፤ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል።