ምዕራፍ 21
1ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱ ስም ሐፍሴባ ነበረ።
2እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበኣል መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም።
4እግዚአብሔርም። ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ።
5በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።
6ልጁንም በእሳት አሳለፈ፥ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤
8ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ።
9ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።
10እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት እጅ እንዲህ ሲል ተናገረ።
11የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ርኵሰት አድርጎአልና፥ ከፊቱም የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና
12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።
13የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።
14የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፥ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤
15አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና።
16ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኃጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።
17የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኃጢአት፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
18ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
19አሞጽም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሜሶላም ነበረች።
20አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ።
21አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ ሰገደላቸውም።
22የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።
23የአሞጽም ባሪያዎች አሴሩበት ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት፥
24የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት።
25የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
26በዖዛም አትክልት ባለው በመቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።