English

ምዕራፍ 22

1ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች።
2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ቀኝም ግራም አላለም።
3በንጉሡም በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፥ እንዲህም አለው።
4የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ።
5በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥
6ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይም ወቃሪዎች፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት።
7ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ነበሩና በእጃቸው ስለ ተሰጠ አይቈጣጠሩአቸውም ነበር።
8ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን፥ የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፥ እርሱም አነበበው።
9ጸሐፊውም ሳፋን ወደ ንጉሡ መጣ፥ ለንጉሡም። በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት፥ በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት ብሎ አወራለት።
10ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው።
11ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
12ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን።
13አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው።
14እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ።
15እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ።
17በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።
18እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥
19እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።
20ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።