English

ምዕራፍ 23

1ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰባቸው።
2ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ።
3ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ።
4ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናትን በረኞቹንም ለባኣልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠላቸው፥ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።
5የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መገጃዎች በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበኣልና ለፀሐይ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትንም አስወገደ።
6የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጣለው።
7ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ።
8ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማይቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማይቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ።
9የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር።
10ማንም ሰው ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዳያሳልፍ በሄኖም ልጆች ሸለቆ የነበረውን ቶፌትን ርኩስ አደረገው።
11የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በጃንደረባው በናታንሜሌክ መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡትን ፈረሶች አስወገደ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ።
12የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፥ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ።
13በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵሰት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵሰት ለአስታሮት ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሚልኮም ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ።
14ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፥ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት።
15ደግሞም በቤቴል የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህን መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው።
16ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በተራራው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ በመሠዊያ አጠገብ ሲቆም እነዚህን ነገሮች የተነባ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ አቃጠላቸው አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዓይኖቹን አቅንቶ።
17ያ የማየው የመታሰቢያ ምልክት ምንድር ነው? አለ። የዚያችም ከተማ ሰዎች። ከይሁዳ ወጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው ብለው ነገሩት።
18እርሱም። ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው አለ፤ እነርሱም ከሰማርያ ከወጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር አጥንቱን ተዉ።
19በሰማሪያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፥ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው።
20በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
21ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ። በዚህ በቃል ኪዳን መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርጉ ብሎ አዘዛቸው።
22እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተፈሰከም።
23ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ።
24ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ።
25እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔርም የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።
26ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም።
27እግዚአብሔርም። እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋላሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና። ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ አለ።
28የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
29በእርሱም ዘመን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው።
30ከሞተም በኋላ ባሪያዎቹ በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፥ በመቃብሩም ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፥ ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት።
31ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
32አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
33በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ባለችው በሪብላ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት።
34ፈርዖን ኒካዑም የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ኢዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብጽ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ።
35ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ይሰጥ ዘንድ ከአገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ።
36ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች።
37አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።