English

ምዕራፍ 6

1በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ።
2በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፥ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር።
3በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን።
4በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ውጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ።
5ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።
6አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን፥ ከዚያ ራቁ፤
7ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው።
8ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ።
9ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው።
10ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው።
11ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ።
12ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።
13ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ።
14የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ።
15ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።
16የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ።
17በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ።
18በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑም በየክፍላቸው አቆሙ።
19ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ።
20ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ።
21ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤
22እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።