ምዕራፍ 7
1ከዚህም ነገር በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥
2የዓዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ የሰሎም ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥
3የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥
4የዘራእያ ልጅ፥ የኦዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥
5የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤
6የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ የሻውን ሁሉ ሰጠው።
7ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም ከሌዋውያኑም ከመዘምራኑም ከበረኞቹም ከናታኒምም በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት አያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።
8በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።
9በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጣ ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።
10ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።
11ንጉሡም አርጤክስስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው።
12ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሙሉ ሰላም ይሁን፤
13በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ የሚወድድ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ።
14በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ትጐበኝ ዘንድ፥
15ንጉሡንና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥
16በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ በንጉሡና በሰባቱ አማካሪዎች ተልከሃልና፤
17ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወደፈኖችንና አውራ በጎችን ጠቦቶችንም የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው።
18ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ።
19ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ።
20ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት አውጣ።
21እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤
22እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ።
23በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ለሰማይ አምላክ ቤት በሙሉ ይደረግ።
24ደግሞም በካህናቱና በሌዋውያን በመዘምራኑም በበረኞቹም በናታኒምም በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይጣል ብለን እናስታውቃችኋለን።
25አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ባሉ ሕዝብ ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ዳኞችንና ፈራጆች አስነሣ፤ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው።
26የአምላክህንም ሕግ፥ የንጉሡንም ሕግ በማያደርግ ሁሉ ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ገንዘብን መወረስ ወይም ግዞት በፍጥነት ይፈረድበት።
27
28በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያሳምር ዘንድ እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ በንጉሡም በአማካሪዎቹም በንጉሡም ኃያላን አለቆች ሁሉ ፊት ምሕረቱን ወደ እኔ የላከ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። እኔም በላዬ ባለችው በአምላኬ በእግዚአብሔር እጅ በረታሁ፤ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል ዘንድ አለቆችን ሰበሰብሁ።