English

ምዕራፍ 28

1ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉ፥ የነገዶቹንም አለቆች፥ ንጉሡንም በክፍል የሚያገለግሉትን የጭፍሮች አለቆች፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆችንም፥ በንጉሥና በልጆች ሀብትና ግዛት ላይ የተሾሙትን፥ ጃንደረቦችንም፥ ጽኑዓን ኃይላኑንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።
2ንጉሡም ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አለ። ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የዕረፍት ቤት ለመሥራት እኔ በልቤ አስቤአለሁ፤ ለሥራም የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤
3እግዚአብሔር ግን። የሰልፍ ሰው ነህና፥ ደምም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም ብሎኛል።
4ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የዘላለም ንጉሥ እሆን ዘንድ ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳም አለቃ ይሆን ዘንድ መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሠኝ ዘንድ ሊመርጠኝ ወደደ።
5እግዚአብሔርም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።
6እርሱም። ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል።
7ትእዛዜንና ፈርዴንም በማድረግ እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘላለም አጸናዋለሁ አለኝ።
8አሁንም የእግዚአብሔር ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር ትወርሱ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ታወርሱአት ዘንድ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፥ ፈልጉም።
9አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።
10አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለመቅደስ የሚሆን ቤትን ትሠራ ዘንድ መርጦሃልና ጠንክረህ ፈጽመው።
11ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ምሳሌውን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው።
12ደግሞም ለእግዚአብሔር ቤት አደባባዮችና በዙርያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት በመንፈሱ ላሰበው ሁሉ ምሳሌን ሰጠው።
13
14የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን በእግዚአብሔርም ቤት በሚያገለግሉበት ሥራ ሁሉ አስታወቀው። በእግዚአብሔርም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤
15ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎችም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩን መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ሁሉ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤
16ለገጹ ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች ሰጠው፤
17ለሜንጦቹና ለድስቶቹ ለመቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን፥ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤
18ለዕጣኑም መሠዊዋ ጥሩውን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሰረገላ ምሳሌ ሰጠው።
19ዳዊትም። የሥራውን ሁሉ ምሳሌ አውቅ ዘንድ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ተጽፎ መጣልኝ አለ።
20ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን። ጠንክር፥ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፥ አትደንግጥም፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፥ አይጥልህምም።
21እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥር በብልሃትና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል አለው።