English

ምዕራፍ 29

1ንጉሡም ዳዊት ለጉባኤው ሁሉ እንዲህ አለ። እግዚአብሔር ብቻውን የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ብላቴና ለጋ ነው፤ ሕንፃው ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክ ነው እንጂ ለሰው አይደለምና ሥራው ታላቅ ነው።
2እኔም እንደ ጕልበቴ ሁሉ ለአምላኬ ቤት ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን፥ ለናሱም ዕቃ ናሱን፥ ለብረቱም ዕቃ ብረቱን፥ ለእንጨቱም ዕቃ እንጨቱን፥ ደግሞም መረግድንና በፈርጥ የሚገባ ድንጋይን፥ የሚለጠፍ ድንጋይን፥ ልዩ ልዩ መልክ ያለውንም ድንጋይ፥ የከበረውንም ድንጋይ ከየዓይነቱ፥ ብዙም እብነ በረድ አዘጋጅቻለሁ።
3ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ።
4የቤቶቹ ግንብ ይለበጡበት ዘንድ ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥
5በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማነው?
6የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ።
7ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና አሥር ሺህ ዳሪክ፥ አሥር ሺህም መክሊት ብር፥ አሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ።
8ዕንቍም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ።
9ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው።
10ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ዳዊትም አለ። አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ።
11አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።
12ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።
13አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።
14ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?
15አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም።
16አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፥ ሁሉም የአንተ ነው።
17አምላኬ ሆይ፥ ልብን እንድትመረምር፥ ቅንነትንም እንድትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ።
18አቤቱ፥ የአባቶቻችን የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ይህን አሳብ በሕዝብህ ልብ ለዘላለም ጠብቅ፥ ልባቸውንም ወደ አንተ አቅና።
19ትእዛዝህንም ምስክርህንም ሥርዓትህንም ይጠብቅ ዘንድ፥ ይህንም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ፥ ያዘጋጀሁለትንም ቤት ይሠራ ዘንድ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው።
20ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባርኩ አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባታቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ባረኩ፥ ራሳቸውንም አዘንብለው ለእግዚአብሔርና ለንጉሡ ሰገዱ።
21በነጋውም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ አንድ ሺህ ወይፈን፥ አንድ ሺህም አውራ በጎች፥ አንድ ሺህም የበግ ጠቦቶች፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም፥ ስለ እስራኤልም ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ።
22በዚያም ቀን በታላቅ ደስታ በእግዚአብሔር ፊት በሉ ጠጡም። የዳዊትንም ልጅ ሰሎሞንን ሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ እርሱንም አለቃ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ቀቡት፥ ሳዶቅንም ካህን ይሆን ዘንድ ቀቡት።
23ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፥ ተከናወነለትም፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት።
24አለቆቹም ሁሉ፥ ኃያላኑም፥ ደግሞም የንጉሡ የዳዊት ልጆች ሁሉ ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ሰጡት።
25እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሁሉ ፊት እጅግ አገነነው፤ ከእርሱ በፊትም ለነበሩት ለእስራኤል ነገሥታት ያልሆነውን የመንግሥት ክብር ሰጠው።
26የእሴይም ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ።
27በእስራኤልም ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ፤ ሰባት ዓመት በኬብሮን ነገሠ፥ ሠላሳ ሦስትም ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ።
28ዕድሜም፥ ባለጠግነትም፥ ክብርም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ልጁም ሰሎሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
29የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል።
30እንደዚሁም የመንግሥቱ ነገርና ኃይሉ ሁሉ በእርሱም በእስራኤልም በአገሮችም መንግሥታት ሁሉ ላይ ያለፉት ዘመናት ተጽፈዋል።