English

ምዕራፍ 18

1በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥
2መልእክተኞችን በባሕር ላይ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣኖች መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደ ሆነ ወገን፥ ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ።
3በዓለም የምትኖሩ ሁሉና በምድር የምትቀመጡ ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በተነሣ ጊዜ እዩ፤ መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ።
4እግዚአብሔር። በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ ብሎኛልና።
5እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ የወይንም ፍሬ ጨርቋ ሲይዝ የወይኑን ዘንግ በማጭድ ይቆርጣል፥ ጫፎቹንም ይመለምላል ያስወግድማል።
6በተራራ ላይ ላሉ ነጣቂዎች ወፎች፥ ለምድርም አውሬዎች በአንድነት ይቀራሉ፤ ነጣቂዎችም ወፎች ይባጁባቸዋል፥ የምድርም አውሬዎች ሁሉ ይከርሙባቸዋል።
7በዚያን ዘመን ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር፥ ከረጅምና ከለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ከሆነ ወገን፥ ከሚሰፍርና ከሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ከሚከፍሉት ሕዝብ ዘንድ እጅ መንሻ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም ወደሚገኝበት ስፍራ ወደ ጽዮን ተራራ ይቀርባል።