English

ምዕራፍ 19

1ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።
2ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።
3የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቍሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ።
4ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል።
6ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ።
7በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም።
8ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ።
9የተበጠረውንም የተልባ እግር የሚሠሩ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ።
10ደገፋዎችዋም ሁሉ ይሰባበራሉ፥ የደመወዘኞችም ነፍስ ትተክዛለች።
11የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቍርና ሆነች። ፈርዖንን። እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ?
12አሁንሳ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ።
13የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ሆነዋል፥ የሜምፎስም አለቆች ተሸንግለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብጽን አሳቱ።
14እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤ ሰካር በትፋቱ እንዲስት እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ አሳቱ።
15ራስ ወይም ጅራት የሰሌን ቅርንጫፍ ወይም እንግጫ ቢሆን ሊሠራ የሚችል ሥራ ለግብጽ አይሆንላትም።
16በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ መንቀሳቀስ የተነሣ ይሸበራሉ ይፈሩማል።
17የይሁዳም ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል።
18በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከነዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።
19በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል።
20ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም መድኃኒትንና ኃያልን ሰድዶ ያድናቸዋልና።
21በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፥ ግብጽAውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቍርባን ያመልካሉ፥ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል።
22እግዚአብሔርም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ እርሱም ይለመናቸዋል ይፈውሳቸውማል።
23በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፥ አሦራዊውም ወደ ግብጽ፥ ግብጻዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብጻውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ።
24
25የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን ብሎ ይባርካቸዋልና በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፥ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል።