English

ምዕራፍ 11

1ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።
2ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ።
3እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፋት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው።
4እንዲህም። ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።
5እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።
6እግዚአብሔርም አለ። እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም።
7ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።
8እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ።
9ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።
10የሴም ትውልድ ይህ ነው። ሴም የመቶ ዓመት ሰው ነበረ፥ አርፋክስድንም ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ወለደ።
11ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
12አርፋክስድም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ቃይንምንም ወለደ፤
13አርፋክስድም ቃይንምን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። ቃይንምም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሳላንም ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን ከወለደ በኋላ ሶስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
14ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ዔቦርንም ወለደ፤
15ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
16ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፥ ፋሌቅንም ወለደ፤
17ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
18ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ራግውንም ወለደ፤
19ራግውንም ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
20ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሴሮሕንም ወለደ፤
21ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
22ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ናኮርንም ወለደ፤
23ናኮርንም ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
24ናኮርም መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ታራንም ወለደ፤
25ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
26ታራም መቶ ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ።
27የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ።
28ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ።
29አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው።
30ሦራም መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም።
31ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ።
32የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።