ምዕራፍ 12
1እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።
2ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤
3የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።
4አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።
5አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ።
6አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ።
7እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና። ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ።
8ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ።
9አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ።
10በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና።
11ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት። አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ
12የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ። ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል።
13እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ። እኅቱ ነኝ በዪ።
14አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤
15የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት።
16ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረገለት፤ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም ነበሩት።
17እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ።
18ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም?
19ለምንስ። እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፤ ይዘሃት ሂድ።
20ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው።