ምዕራፍ 23
1የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ።
2በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።
3አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፥
4ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ። እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር።
5የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም።
6ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ፤ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።
7አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ ለኬጢ ልጆች፥ ሰገደ።
8እንዲህም አላቸው። ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤
9በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን።
10ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
11አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፤ እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።
12አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤
13የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ። ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፤ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።
14ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።
15ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር።
16አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው፤ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ።
17በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤
18እርሻው በእርሱም ያለው ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ።
19ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ።
20እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።