ምዕራፍ 24
1አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው።
2አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው።
3እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤
4ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ።
5ሎሌውም። ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን? አለው።
6አብርሃምም አለው። ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤
7ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ። ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ።
8ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው።
9ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት።
10ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስጼጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ።
11ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ።
12እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ።
13እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤
14ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።
15ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት።
16ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች።
17ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት።
18እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው።
19እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች።
20ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች።
21ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ።
22ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤
23እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን?
24አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ።
25በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን።
26ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ ።
27እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።
28ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች።
29ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ።
30ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር። ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር።
31እርሱም አለው። አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ።
32ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ።
33መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን። ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። እርሱም። ተናገር አለው።
34እርሱም አለ። እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ።
35እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው።
36ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው።
37ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ። እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ
38ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት።
39ጌታዬንም። ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት።
40እርሱም አለኝ። አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል። ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤
41የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ።
42ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤
43እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ። ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥
44እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን።
45እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም። እስኪ አጠጪኝ አልኋት።
46ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች።
47እኔም። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም። ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት።
48በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ።
49አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ።
50ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም።
51ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን።
52የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ።
53ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ።
54እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፤ ማልደውም ተነሡና። ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው ።
55ወንድምዋና እናትዋም። ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች አሉ።
56እርሱም። እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው።
57እነርሱም። ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ።
58ርብቃንም ጠርተው። ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም። እሄዳለሁ አለች።
59እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው።
60ርብቃንም መረቁአትና። አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት።
61ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ።
62ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፤ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና።
63ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ።
64ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች።
65ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች።
66ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው።
67ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። a