English

ምዕራፍ 25

1አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ።
2እርስዋም ዘምራንን፥ ዮቅሳንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የስቦቅን፥ ስዌሕን ወለደችለት።
3ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን፥ ለጡሳውያን፥ ለኡማውያን ናቸው።
4የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።
5አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤
6የአብርሃምም ለነበሩ ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው።
7አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ።
8አብርሃምም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካም ሽምግልናም ሞተ፤ ሸመገለም፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
9ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት ።
10አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ።
11አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ።
12የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤
13የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ
14ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥
15ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ።
16የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው።
17እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞተም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
18መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ።
19የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤
20ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፤ እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት።
21ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች።
22ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም። እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች።
23እግዚአብሔርም አላት። ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።
24ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ።
25በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ።
26ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
27ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር።
28ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፥ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች።
29ያዕቆብም ወጥ ሠራ፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤
30ዔሳውም ያዕቆብን። ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው፤ ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ።
31ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው።
32ዔሳውም። እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ ።
33ያዕቆብም። እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ።
34ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት።