ምዕራፍ 44
1ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘ። ዓይበታቸው የሚያነሣውን ያህል እህል ሙላላቸው፥ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤
2በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው። እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ።
3ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ ተሰናበቱ።
4ከከተማይቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ። ተነሥተህ ሰዎቹን ተከተላቸው፤ በደረስህባቸውም ጊዜ እንዲህ በላቸው። በመልካሙ ፋንታ ስለ ምን ክፉን መለሳችሁ?
5ጌታዬ የሚጠጣበት ምሥጢርንም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ።
6እርሱም ደርሰባቸው ይህንም ቃል ነገራቸው።
7እነርሱም አሉት። ጌታዬ እንደዚህ ያለውን ቃል ለምን ይናገራል? ባሪያዎችህ ይህን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም።
8እነሆ፥ በዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር ይዘን ከከነዓን አገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን?
9ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን ባሪያዎች እንሁን።
10እርሱም አለ። አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ ባሪያ ይሁነኝ፥ እናንተም ንጹሐን ትሆናላችሁ።
11እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፥ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ።
12እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፥ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው።
13ልብሳቸውንም ቀደዱ፥ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ።
14ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፥ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ።
15ዮሴፍም። ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድር ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን? አላቸው።
16ይሁዳም አለ። ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ፤ እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበቱም ደግሞ ለጌታዬ ባሪያዎቹ ነን።
17እርሱም እላቸው። ይህን አደርግ ዘንድ አይሆንልኝም፤ ጽዋው የተገኘበቱ ሰው እርሱ ባሪያ ይሁነኝ፤ እናንተም ወደ አባታችሁ በደኅና ውጡ።
18ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ እንዲህም አለ። ጌታዬ ሆይ፥ እኔ ባርያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና።
19ጌታዬ ባሪያዎቹን። አባት አላችሁን ወይስ ወንድም? ብሎ ጠየቀ።
20እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልነ። ሸማግሌ አባት አለን፥ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙም ሞተ፥ ከእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፥ አባቱም ይወድደዋል።
21አንተም ለባሪያዎችህ። ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም አየዋለሁ አልህ።
22ጌታዬንም። ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልነው።
23ባርያዎችህንም። ታናሽ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኽን።
24ወደ ባርያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታዬን ቃል ነገርነው።
25አባታችንም። ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለ።
26እኛም አልነው። እንሄድ ዘንድ አይሆንልንም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ይወርድ እንደ ሆነ እኛም እንወርዳለን፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና።
27ባሪያህ አባቴም እንዲህ አለን። ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤
28አንዱም ከእኔ ወጣ። አውሬ በላው አላችሁኝ፥ እስከ ዛሬም አላየሁትም፤
29ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።
30አሁንም እኔ ወደ አባቴ ወደ ባሪያህ ብሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ባየ ጊዜ ይሞታል፤
31ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ።
32እኔ ባሪያህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና። እርሱንስ ወደ አንተ ባላመጣው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኃጢአተኛ እሆናለሁ።
33ስለዚህም እኔ ባሪያህ በጌታዬ ዘንድ ባሪያ ሆኜ በብላቴናው ፋንታ ልቀመጥ፤ ብላቴናውም ከወንድሞቹ ጋር ይውጣ።
34አለዚያም ብላቴናው ከእኔ ጋር ከሌለ ወደ አባቴ እንዴት እወጣለሁ? አባቴን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ። a