English

ምዕራፍ 45

1ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም። ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም።
2ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ።
3ዮሴፍም ለወንድሞቹ። እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና።
4ዮሴፍም ወንድሞቹን። ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው። ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ።
5አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና።
6ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ።
7እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ።
8አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ።
9አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት። ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው። እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤
10በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፥ ወደ እኔም ትቀርባለህ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ።
11በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና።
12እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል።
13ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።
14የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ።
15ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።
16በፈርዖንም ቤት። የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ በዚያውም ፈርዖንና ሎላልቱ ደስ ተሰኙበት።
17ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ይህን አድርጉ፤ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤
18አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።
19አንተም ወንድሞችህን። እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤
20ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።
21የእስራኤል ልጆችም እንደዚሁ አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤
22ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፥ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው።
23ለአባቱም እንደዚሁ ሰደደ፥ የግብፅን በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን።
24ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው። በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።
25እነርሱም ሄዱ፥ ከግብፅ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ።
26እንዲህም ብለው ነገሩት። ዮሴፍ ገና በሕይወቱ ነው፥ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ አላመናቸውም ነበርና።
27እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት፤ እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደሰች።
28እስራኤልም። ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።