English

ምዕራፍ 6

1እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤
2የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።
3እግዚአብሔርም። መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ።
4በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ።
5እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።
6እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ።
7እግዚአብሔርም። የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ።
8ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።
9የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።
10ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።
11ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።
12እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና።
13እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።
14ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፥ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።
15እርስዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን።
16ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመትዋም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ።
17እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል።
18ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ።
19ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን።
20ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ።
21ከሚበላውም መብል ሁሉ ለአንተ ውሰድ፥ ወደ አንተም ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተም ለእነርሱም መብል ይሆናል።
22ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።