ምዕራፍ 7
1እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።
2
3ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባትና እንስት፥ ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ።
4ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና።
5ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ።
6ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።
7ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ።
8ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥
9እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።
10ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ።
11በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤
12ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ።
13በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ።
14እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥
15ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።
16ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት።
17የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ፤ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች።
18ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች።
19ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።
20ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ተራሮችም ተሸፈኑ።
21በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ።
22በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።
23በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ።
24ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።