ምዕራፍ 104
1ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለበስህ።
2ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፤ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ፤
3እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥
4መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል።
5ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት።
6በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።
7ከዘለፋህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነግጣሉ፤
8ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፤
9እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ።
10ምንጮችን ወደ ቈላዎች ይልካል፤ በተራሮች መካከል ውኆች ያልፋሉ፤
11የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማታቸውን ይረካሉ።
12የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በድንጋዩ ስንጥቅ መካከልም ይጮኻሉ።
13ተራሮችን ከላይ የሚያጠጣቸው፤ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች።
14እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፥ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል።
15ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።
16የእግዚአብሔር ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ።
17በዚያም ወፎች ይዋለዳሉ፥ የሽመላ ቤትም የእነርሱ ጎረቤት ነው።
18ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው።
19ጨረቃን ለጊዜዎች አደረገ፤ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል።
20ጨለማ ታደርጋለህ ሌሊትም ይሆናል፤ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል።
21የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ።
22ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ በየዋሻቸውም ይተኛሉ።
23ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል።
24አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።
25ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤ በዚያ ስፍራ ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።
26በዚያ ጊዜ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ይጫወትበታል።
27ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
28በሰጠሃቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፤ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ።
29ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፤ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ።
30መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።
31የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይሁን፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል።
32ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፤ ተራሮችን ይዳስሳል ይጤሳሉም።
33በሕይወቴ ሳለሁ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ።
34ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል።
35ኅጥኣን ከምድር ይጥፉ፤ ዓመፀኞች እንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።