English

ምዕራፍ 105

1እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ።
2ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ።
3በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።
4እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።
5
6ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱን የአፉንም ፍርድ።
7እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው።
8ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥
9ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤
10ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና።
11እንዲህም አለ። ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤
12ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው።
13ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ።
14-
15የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።
16በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ።
17በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ።
18እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ።
19ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።
20ንጉሥ ላከ ፈታውም፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው።
21የቤቱ ጌታ፥ የጥሪቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥
22አለቆቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ።
23እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ።
24ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው።
25ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ።
26ባሪያውን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ።
27የተኣምራቱን ነገር በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረገ።
28ጨለማን ላከ ጨለመባቸውም፤ በቃሉም ዐመፁ።
29ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ።
30ምድራቸው የንጉሦቻቸውም ቤቶች በጓጕንቸር ሞሉ።
31ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በዳርቻቸው መጡ።
32ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ተቃጠለች።
33ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ።
34ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥
35የአገራቸውንም ለምለም ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ።
36የአገራቸውንም በኵር ሁሉ፥ የጕልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ።
37ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ ደዌ አልነበረም።
38ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት።
39ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ።
40ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው።
41ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈሰሰ፤ ወንዞች በበረሃ ሄዱ፤
42ለባሪያው ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስቦአልና።
43ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ።
44የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ የወገኖችንም ድካም ወረሱ፥
45ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ