ምዕራፍ 114
1እስራኤል ከግብጽ፥ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ ሕዝብ በወጣ ጊዜ፥
2ይሁዳ መቅደሱ፥ እስራኤልም ግዛቱ ሆነ።
3ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።
4ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ።
5አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል?
6እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ?
7ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት ምድር ተናወጠች፤
8ድንጋዩን ወደ ውኃ መቆሚያ፥ ጭንጫውንም ወደ ውኃ ምንጭ ከለወጠ።