ምዕራፍ 115
1ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥ ነገር ግን ለስምህ ስለ ምሕረትህ ስለ እውነትህም ምስጋናን ስጥ።
2አሕዛብ። አምላካቸው ወዴት ነው? አይበሉ።
3አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፤ በሰማይም በምድርም የፈቀደውን ሁሉ አደረገ።
4የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው።
5አፍ አላቸው አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው አያዩምም፤
6ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፤
7እጅ አላቸው አይዳሰሱምም፤ እግር አላቸው አይሄዱምም፤ በጕሮሮአቸውም አይናገሩም።
8የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።
9የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
10የአሮን ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
11እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው።
12እግዚአብሔር አሰበን ይባርከንማል፤ የእስራኤልን ቤት ይባረካል፥ የአሮንንም ቤት ይባረካል።
13እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ትንንሾችንና ትልልቆችን ይባርካል።
14እግዚአብሔር በላያችሁ፥ በላያችሁና በልጆቻችሁ ላይ ይጨምር።
15እናንተ ሰማይንና ምድርን ለሠራ ለእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ።
16የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።
17አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፤
18እኛ ሕያዋን ግን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔርን እንባርካለን። ሃሌ ሉያ።